የሲኦል ምንነት
ሲኦል የት ነው?
ወደ ሲኦል የሚወስደው መንገድ
ወደ ሲኦል የሚገባው ማን ነው?
የጠፉት በሲኦል ምን ይሆናሉ?
እግዚአብሔር ኃጢአተኛን ይቀጣ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዘላለማዊው የእሳት ባህር አሰቃቂነት እውነታ በግልጽ ያስተምራል፡፡ ኃጢአተኛ ሰው እግዚአብሔር በሰጠው ጊዜ ውስጥ ንስሐ ገብቶ ከዚህ አሰቃቂ ኩነኔ እንዲያመልጥ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡
የሲኦል ምንነት
ሲኦል የእሳት ባሕር ነው (ራእይ 20፥14)፡፡ ዘላለማዊ ድቅድቅ ጨለማ ነው (ይሁዳ 13)፡፡
“የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው……..ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ” (ራእይ 9፥1-2)፡፡
“እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል። የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል………..ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም” (ራእይ 14፥10-11)፡፡
ሲኦል የት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ሲኦል ከእግዚአብሔር የራቀና በታች፣ በጥልቁ የሚገኝ ቦታ እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡ “በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል” (ምሳሌ15፥24)። “ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ” (ማቴዎስ 11፥23)። “ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል” (ሉቃስ 16፥26)።
ወደ ሲኦል የሚወስደው መንገድ
“በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው” (ማቴዎስ 7፥13)። በመጀመሪያ ይህንን መንገድ ለማግኘት ቀላል ነው ምክንያቱም “ሰፊ ደጅ” ነውና፡፡ ሁለተኛ በመንገዱ ላይ ለመጓዝ ከባድ አይደለም ምክንያቱም “መንገዱ ትልቅ ነውና”፡፡ ሶስተኛ “ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸውና” በተጓዦች የተሞላ መንገድ ነው።
ወደ ሲኦል የሚገባው ማን ነው?
“ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ” (መዝሙር 9፥17)። “ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ……እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል…….ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ”(2ኛ ተሰሎንቄ 1፥7-8)።
“በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ” (ራእይ 20፥15)። “የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው” (ራእይ 21፥8)።
“በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” (ማቴዎስ 25፥41-46)።
የጠፉት በሲኦል ምን ይሆናሉ?
በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆንባቸዋል (ማቴዎስ 22፥13)። ማብቂያ በሌለውና ሊነገር በማይችል ስቃይ ውስጥ ሆነው በመንግስተ ሰማይ የሚኖሩ የዳኑ ቅዱሳንን መጽናናትና ደስታ ያያሉ። “በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል” (ማቴዎስ 22፥13)። “በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ” (ሉቃስ 16፥23-24)።
እግዚአብሔር ኃጢአተኛን ይቀጣ ይሆን?
“እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው…..በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” (2ኛ ጴጥሮስ 2፥4፣5፣9-10)።
አዎ፣ ኃጢአትና መተላለፍ ሁሉ ብድራትን ይቀበላል።
የማታምን፣ የምታክፋፋ፣ ሀፍረተ ቢስ፣ የማትታመን፣ የዝሙትና የሆድህ ባሪያ የሆንክና በእግዚአብሔር እውነት ላይ የምትዘብት ከሆንክ “ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣለህ?” (ማቴዎስ 23፥33)። ነብስህ ትርፍን በማጋበስ የተለከፈች ከሆነ፣ እውነተኛው የእግዚአብሔር ሀብት የሌለህ ባለጠጋ ከሆንክ፣ የማትጸልይ የሕይወት ተጓዥ ከሆንክ፣ ዘላለማዊ ሀብት ለሆነው እግዚአብሔርና ለዘላለማዊ ሕይወት ደንታ ቢስ ሰው ከሆንክ- ስማ! “ሲኦልም ሆድዋን አስፍታለች፥ አፍዋንም ያለ ልክ ከፍታለች ከበርቴዎቻቸውና አዛውንቶቻቸው ባለጠጎቻቸውም ደስተኞቻቸውም ወደ እርስዋ ይወርዳሉ” (ኢሳይያስ 5፥14)።
እውነተኛ ክርስቲያን ለመሆን እየፈለክ ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግስት ደጃፍ ላይ ቆመህ የምትወላውል ከሆነ፤ ለመግባት ዝግጁ ሳትሆን ቀርተህ በደጃፉ አሻግረህ እየተመለከትክ ከሆነ፤ እየፈለክ የማታደርግ፤ እየተመኘህ በቀጠሮ የምታልፍ፤ በተስፋ ብቻ ካለህ “እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?” (ዕብራውያን 2፥2) የሚለው ማስጠንቀቂያ ላንተ ነው።
ቃል ኪዳኑን የረሳ ክርስቲያን ከሆንክና የኃጢአትንና የሞትን ሰፈር ለቀህ እየወጣህ ሳለ በማመንታት ቆም ብለህ ወደ ኋላህ እያየክ ከሆነ “የሎጥን ሚስት አስብ” (ሉቃስ 17፥32)። የኃጢአተኞች ፍርድ ከጥንት ጀምሮ እንደማይዘገይ ጥፋታቸውም እንደማይንቀላፋ (2ኛ ጴጥሮስ 2፥3) ታስተውላለህን? “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደ ሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” (ዮናስ 1፥6) የሚለው መልዕክት ዛሬ ወደአንተ እየመጣ ነው።
ኦ እናንተ ያልዳናችሁ ሁሉ፣ ዛሬውኑ ፊታችሁን ወደ ጌታ መልሱ። “እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ” (ኢሳይያስ 55፥6-7)።